
Ethiopian writer and activist Befeqadu Hailu has been awarded the 2019 PEN Pinter Prize for an International Writer of Courage. He delivered the following acceptance speech at an unforgettable ceremony at the British Library, alongside Lemn Sissay, on 10 October 2019
Ladies and Gentlemen.
I am extremely excited to stand before you today, thanks to Lemn Sissay, as if I were a brave person with the title of ‘Writer’. To be honest, I don’t consider myself to be a brave writer. I am not very comfortable with words like bravery and heroism, as they seem to me some sort of chauvinism embedded in masculinity.
I believe that the source of my writings is fear. I grew up in a social environment where abject poverty and illiteracy were rampant. I understand these two factors as evils. They scare me, always. Thus, I write – consciously or unconsciously – out of fear for them. I write particularly to escape injustice, the first child of poverty and ignorance.
I have faced repeated persecution for writing or speaking out. I was detained four times for no crime before eventually being acquitted. As a result, 596 days of my life have been wasted in prison. I have been a victim of surveillance, intimidation, beatings and insults. But I can say confidently that I have gained rather than lost by writing.
I don’t say this driven by self-importance, counting prizes I have collected or acclamations I have enjoyed.
Of course, ‘Children of Their Parents’, my novella in basic English, once earned me good money and recognition. And, since then, international organisations such as the Committee to Protect Journalists, Human Rights Watch, Reporters Without Borders and other human rights defenders have credited me for my work as a member of the Zone 9 Bloggers. And I must admit that people in Addis Ababa energise me when they stop me in the street and say, ‘Hey man, you and your likes inspire us to put hope in our country and the generation’.
However, it is my writings that help me more than anything else to know myself, to feel myself. Nebiy Mekonnen, an Ethiopian poet, once wrote: ‘When I am sick inside, I cure myself of the illness by writing’.
Writing has helped me to know what I don’t know, to have the courage to try what I fear, to examine what I don’t understand. My pain is not mine alone; my writing has shown me this. I can’t count how many times I have heard the expression ‘You spoke my mind’. Writing has helped me to observe that thousands of Ethiopians, and people elsewhere, share my pain.
I had to read in order to write. I have read to learn, to accept – and not to accept. There have been times when I have started writing to argue with others, and then found myself arguing with myself.
Being imprisoned for my writing was not that injurious. The arrest of my friends and I unveiled to the public the wicked side of the regime in power, and became part of a wider campaign for freedom. The fact that we were suppressed for simply exercising our natural rights only made us more aware of those who have been deprived of their liberty. I believe we have become more vocal and better advocates since.
Writing is like using a sharp knife with two edges. It sharpens both the writer and their audience. In the era of social media, it is easy to receive immediate feedback. Like the law of physics that assumes equal or proportional reaction for every action, I receive feedback for every piece I write. I have been insulted for what I have written. Sometimes, the comments I have received have made me feel I have written on something I don’t know about. Sometimes, I have received threats.
But importantly, the feedback means I am forced to live the life that I preach. The process is ongoing, and I believe it makes me a better person. And if my writing has helped others – which I believe it has – then that is my dividend.
I think the freedom to write or speak is an intermediary path between change and violence. Many writers disdain violence. And yet they shape a better world when they write bitter truths and encourage audiences to leave their comfort zones. No war, no force, no campaign has as much power to change the world without claiming lives as writing.
As I understand the magnitude of the power of writing, I continue to overcome my fears. I will speak and write whenever opportunity is at hand. I now contribute weekly articles for a newspaper published in Ethiopia and for Deustche Welle Amharic. I am offered the chance because I dared to write, to defeat fear. I tell all who ask that I have more than one voice in my country.
My wish is to use my voices for the service of the suppressed, those who are victimised because of sexual orientation, creed, religion or political opinion. My dream will come true. My wish is to give my voice to the service of the voiceless, who spoke for me when I could not. I pay it back only when I write to become a voice for the voiceless, the unheard.
The recognition I am offered today, on this stage, makes it possible to use my voice for good. I thank you so much. I dedicate this prize to all those who use their voices for the voiceless.
Translated from Amharic by Dejene Tessema
ክቡራት እና ክቡራን፣
ለምን ሲሳይ ምሥጋና ይግባውና፣ ዛሬ ከፊታችሁ ቆሜ “በድፍረት የጻፈ ሰው” የሚል ማዕረግ በማግኘቴ የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ
ግን ራሴን እንደ ደፋር ጸሐፊ አልቆጥርም። ይልቁንም ደፋርነት እና ጀግንነት በተባዕታዊ ትዕቢት የታጀቡ ስለሚመስሉኝ አልወዳቸውም።
የኔ ጽሑፎች ሁሉ ምንጫቸው ፍርሐት ነው ብዬ አምናለሁ። በአስከፊ ድህነት እና መሐይምነት በተንሰራፋበት ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ እንደማደጌ፣
አሰቃቂነታቸውን እረዳለሁ እና ዘወትር እፈራቸዋለሁ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የምጽፈው እነርሱን ፈርቼ ነው። ከድህነት እና ከድንቁርና
በተለይ በተለይ ደግሞ የድህነት እና የድንቁርና የበኩር ልጅ የሆነው ኢፍትሐዊነትን ለማምለጥ ስለምፈልግ እጽፋለሁ።
በመጻፌ ወይም በመናገሬ ምክንያት ተደጋጋሚ እንግልት ደርሶብኛል።
አራት ጊዜ ያህል ያለጥፋቴ ታስሬ በነጻ ተፈትቻለሁ። በዚህ ሳቢያ ከሕይወቴ 596 ቀናት በእስር ባክነዋል። ክትትል እና ማጉላላት፣
ድብደባ እና ስድብ ደርሶብኛል። ነገር ግን በጽሑፍ ከተጎዳሁት ይልቅ የተጠቀምኩት እንደሚበልጥ ስነግራችሁ በልበ ሙሉነት ነው። የተጠቀምኩት
የምለው የተሸለምኳቸውን ሽልማቶች እና የቀረቡልኝን ሙገሳዎች አስቤ አይደለም። እርግጥ ነው፣ በአንድ ወቅት “ችልድረን ኦቬ ዜር
ፓረንትስ” በሚል ርዕስ በተለማማጅ እንግሊዝኛዬ የጻፍኩት ልቦለድ የበኩሬ የሆነውን የገንዘብም የማዕረግም ሽልማት አስገኝቶልኛል፤
ከዚያ በኋላም ሲፒጄ፣ ሒዩማን ራይትስ ዎች፣ ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ከዞን ዘጠኝ የጦማሪዎች
እና የመብት ተሟጋቾች ስብስብ ቡድን ጋር ለሠራነው ሥራ ዕውቅና ሰጥተውናል። አንዳንድ ሰዎች አዲስ አበባ መንገድ ላይ እያስቆሙኝ
“የአንተና መሰሎችህ መኖር በአራችን እና በትውልዳችን ተስፋ እንድናደርግ ረድቶናል” ሲሉኝ ልብ የሚያሞቅ ውዳሴያቸው እንዳልደክም
ገፊ ምክንያት እንደሆነኝ አልሸሽጋችሁም። ሆኖም ግን ከሁሉም በበለጠ ተጠቅሜበታለሁ የምለው ራሴን በራሴ ጽሑፎች መለወጥ በመቻሌ
ነው።
ነብይ መኮንን የተባለ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ ለምን እንደሚጽፍ በቅኔ
ሲናገር “ውስጤን ሲያመኝ፣ በጽሑፍ አክመዋለሁ” ብሎ ነበር። መጻፍ የማላውቀውን እንዳውቅ፣ የምፈራውን እንድደፍር፣ ያልገባኝ እንዲገባኝ
አድርጓል። ለካስ የኔ ሕመም የኔ ብቻ አልነበረም። ለካስ የኔ ብሶት የኔ ብቻ አልነበረም፤ መጻፍ ነው ይህንን ፍንትው ባለ መንገድ
ያስረዳኝ – “የልቤን ነው የገለጽክልኝ” የሚለውን አስተያየት ስንት ጊዜ እንደሰማሁት መቁጠር አልችልም። መጻፌ የኔን ችግር የሚጋሩ
እልፍ ኢትዮጵያውያን አልፎ ተርፎም ዓለማውያን እንዳሉ እንዳስተውል ረድቶኛል።
ለመጻፍ ማንበብ ነበረብኝ፣ በማንበብም ያልገባኝን ከመረዳቴም
በላይ አንዳንዴ ልቀበላቸው የሚቸግሩኝን እውነታዎች ተጋፍጫለሁ። ሌሎችን ልከራከር መጻፍ ጀምሬ ክርክሩ ከገዛው ራሴ ጋር ሆኖ ያገኘሁበት
ጊዜ አለ። ሌላው ቀርቶ በመጻፌ ምክንያት መታሰሬ በራሱ ጉዳት ብቻ አልነበረውም። እንዲያውም፣ እኔና ጓደኞቼ መታሰራችን የመንግሥትን
ገመና በአደባባይ ስለሚያውለው ራሱን የቻለ የነጻነት ዘመቻ አድርገን ነበር የምናየው። ከዚያም በላይ ተፈጥሯዊ መብታችንን ብቻ በመተግበራችን
ምክንያት መታፈናችን ነጻነታቸው ከተረገጡ ወገኖች ጎን መቆም የሚሰጠውን ስሜት የበለጠ እንድንረዳ አድርጎናል። ከእስር በኋላ የተሻለ
ስለ መብቶች ተቆርቋሪ፣ የተሻለ ስለጭቁኖች ተቆርቋሪ ሆነናል ብዬ አምናለሁ።
መጻፍ በሁለት በኩል ስለት ያለው ቢላዋ እንደመጠቀም ነው።
ጸሐፊውንም ተደራሲውንም ነው በአንድ ላይ የሚስለው። በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን እየጻፉ ምላሹን ሳይሰሙ መቅረት አይቻልም።
የፊዚክሱ ሕግ ለእያንዳንዱ ገቢር፣ እኩል እና ተመጣጣኝ ድኅረ ገቢር አለው እንደሚለው ሁሉ፣ ለእያንዳንዱ ጽሑፍ ተመጣጣኝ ምላሽ
መቀበል ነበረብኝ። በጽሑፎቼ ብዙ ጊዜ ተሰድቤያለሁ፣ ከሚደርሱኝ አስተያየቶች ስለማላውቀው ነገር እየጻፍኩ እንደሆነ ተሰምቶኝ ያውቃል፣
ማስፈራሪያዎች ደርሰውኛል። ከዚያም በላይ በጽሑፌ የምሰብከውን ዓይነጽ ምናባዊ ሕይወት በተግባር ለመኖር ለመጣር ተገድጃለሁ። ሒደቱ
ቀጣይ ነው፤ የተሻለ ሰው እያደረገ እየቀረጸኝም ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ተርፎ የጠቀማቸው ሰዎች ካሉ – አሉም ብዬ አምናለሁ
– ለኔ የትርፍ ትርፍ ነው።
የመጻፍ ወይም የመናገር ነጻነት በነውጥ እና ለውጥ መካከል
አስታራቂ መንገድ ይመስለኛል። ብዙዎቹ ጸሐፊዎች ነውጥን ይጸየፋሉ። ነገር ግን መራር እውነቶችን እየጻፉ እና ተደራሲዎች ከምቾት
ዞናቸው ወጥተው እንዲያስቡ በማደፋፈር የወደፊቷን ዓለም ይቀርጻሉ። የትኛውም ጦርነት፣ የትኛውም ኀይል፣ የትኛውም ዘመቻ የጽሑፍ
ዘመቻን ያህል አንድም ነፍስ ሳያጠፋ ዓለምን የመቀየር ኀይል የለውም።
ይህንን የጽሑፍ ኀይል በመረዳቴ ምክንያት ፍርሐቴን እያሸነፍኩ
መጻፌን ቀጥያለሁ። በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ እናገራለሁ፣ እጽፋለሁም። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታተም አንድ ጋዜጣ እና ለጀርመን
ድምፅ የአማርኛ ዜና ድረገጽ ሳምንታዊ ጽሑፎችን አበረክታለሁ። ይህም ከፍርሐቴ እየታገልኩ በመጻፌ ያተረፍኩት ዕድል ነው። ስለዚህ
ጉዳይ ለሚጠይቁኝ ሰዎች ሁሉ “እኔ በአገሬ ከአንድ ሰው በላይ ድምፅ አለኝ” እያልኩ እናገራለሁ። የወደፊት ምኞቴ ከአንድ ሰው በላይ
የሆነውን ድምፄን መብታቸው ለተረገጡ ሕዝቦች፣ በማንነታቸው፣ በስርዓተ ፆታቸው፣ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ
ሰዎች አገልግሎት ማዋል ነው። ያኔ ሕልሜ እውን ይሆናል። እኔ ድምፅ አልባ በሆንኩበት ሰዓት ለተናገሩልኝ ሰዎች ውለታቸውን የምከፍለው
ስለ ድምፅ አልባዎች እና አድማጭ ያጡ ሰዎችን ድምፅ መሆን የሚችሉ ጽሑፎችን መጻፍ የቻልኩ ጊዜ ነው።
ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ የተሰጠኝ ዕውቅና እና ሌሎችም ድምፄን፣
እንዲሁም ጽሑፎቼን ለበጎ ዓላማ እንዳውለው ስለሚያደርገኝ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ። መታሰቢያነቱም ድምፃቸውን ለድምፅ አልባዎች ለሚያውሉ
ሰዎች ይሁንልኝ።